በ”ካማ” አማካኝነት ስምንት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያውያን አንትረፕረነርስ፣ ስታርትአፕዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ሀገር በቀል መፍትሔዎችን እንዲያዳብሩ፣ በተግባር እንዲፈትሹና ወደ ገበያ እንዲያሸጋግሩ ዕድል ይፈጥራል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (ኢኢሆ) ከኤ.ኤል.ኤክስ ኢትዮጵያ (ALX Ethiopia) ጋር በመተባበር፣ የሀገራችን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያውያን አንትረፕረነርዎች፣ ስታርትአፕዎች (Startups) እና የፈጠራ ባለሙያዎች ጋር የሚያገናኘውን “ካማ” የተሰኘ ቁልፍ የኦፕን ኢኖቬሽንና የቬንቸር ቢልዲንግ መርሐ-ግብር ዛሬ ይፋ አስጀምሯል።
የመርሐ-ግብሩ ይፋ መሆን ለ”ካማ” የመጀመሪያ ዙር ምዝገባ መከፈቱን የሚያበስር ሲሆን፣ በዚህ ዙር ስምንት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሙያዎች መፍትሔ እንዲያመጡባቸው የሚፈልጓቸውን ተጨባጭ የንግድና የአሠራር ፍላጎቶች ያቀርባሉ።
ኢትዮጵያ ተጨባጭ ችግሮችን መፍታትና አዳዲስ ዕድሎችን መፍጠር የሚችሉ ብሩህና የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች አሏት። ሆኖም ተስፋ ሰጪ ሀሳቦች ወደ ገበያ ቀርበው ለማደግ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት፣ ተቋማዊ ድጋፍና የገበያ ትስስር ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ይቸገራሉ። በሌላ በኩል፣ የሀገሪቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተደራጀ መሠረተ ልማት፣ የስርጭት መረብና ሰፊ የገበያ ተደራሽነት ያላቸው ቢሆንም፣ በፍጥነት እየተለወጠ በመጣው የቴክኖሎጂ ዓለም ተወዳዳሪ ሆነው ለመቀጠል ይበልጥ ቀልጣፋ የአሠራር ዘይቤና ዲጂታል ብቃት ያስፈልጋቸዋል። “ካማ” እነዚህን ሁለት አካላት በማገናኘት የሀገሪቱን የፈጠራ ሥነ-ምህዳር ለማሳደግ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።
በ”ካማ” መርሐ-ግብር አማካኝነት እያንዳንዱ ተሳታፊ የመንግሥት የልማት ድርጅት መፍትሔ የሚፈልጉ ተጨባጭ የንግድና የአሠራር ችግሮቹን በመለየት አሠራሩን ለኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሙያዎች ክፍት ያደርጋል። የተመረጡ የተመረጡ ስታርትአፕዎችና ባለሙያዎች ከተቋማቱ ባለሙያዎች ጋር በመሆን መፍትሔዎችን በተጨባጭ የሥራ ከባቢ ውስጥ ይነድፋሉ፣ በተግባር ይፈትሻሉ፣ ያሻሽላሉ። የልማት ድርጅቶቹም የመጀመሪያ ደንበኛና አብረው እሴት የሚፈጥሩ አጋሮች በመሆን ይሳተፋሉ።
መርሐ-ግብሩ በአራት ዙሮች የሚተገበር ሲሆን፣ ተስፋ ሰጪ ሀሳቦችን ከመጀመሪያ ደረጃ ዝግጅትና ሙከራ ጀምሮ ወደ አዋጭ የንግድ ዕድል፣ የገበያ ማስገባትና ማስፋት ያሸጋግራል።
“ካማ” ሀገር በቀል መፍትሔዎችንና ስታርትአፕዎችን በማገዝና ወደ ገበያ የማሸጋገር ሂደትን ለማፋጠን ያለመ ነው። በተጨማሪም የሀገር ውስጥ የፈጠራ ባለሙያዎች የሀገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያሳድጉ ዲጂታልና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያበለጽጉና በተግባር እንዲያውሉ ዕድል በመፍጠር ለ«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ግቦች መሳካት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል።
እንዴት ማመልከት ይቻላል?
የ”ካማ” የመጀመሪያ ዙር (Cohort 1) ማመልከቻ ከኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ 29 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል። መስፈርቱን የሚያሟሉ አንትረፕረነርስ፣ ስታርትአፕዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች የልማት ድርጅቶቹ ያቀረቧቸውን የፈጠራ ፍላጎቶች (Challenge Statements) በመመልከት በwww.kama.et አማካኝነት ማመልከቻቸውን በኦንላይን ማስገባት ይችላሉ። ስለሚካሄዱት የመረጃ መስጫ መድረኮችም ዝርዝር መረጃ በዚሁ ድረ-ገጽ ላይ ይገኛል።
ስለ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH)
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ሀብት የመገንባት ተልዕኮ የተሰጠው የአፍሪካ የሉዓላዊ ሀብት ፈንድ ነው። በተጨማሪም ዘመናዊ የአስተዳደር አሠራሮችን፣ ጠንካራ የድርጅታዊ አስተዳደር መርሆችን እና ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንቶችን በመተግበር በሥሩ የሚገኙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን እና የንግድ ሀብቶችን አፈጻጸምና እሴት የማሳደግ፣ እንዲሁም በፈጠራ መድረኮች እና ለውጥ አምጪ አጋርነቶች አማካኝነት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ዘላቂ ልማት የማረጋገጥ ተልዕኮ ተሰጥቶታል።
ስለ ኤ.ኤል.ኤክስ ኢትዮጵያ (ALX Ethiopia)
ኤ.ኤል.ኤክስ ኢትዮጵያ (ALX Ethiopia) የአፍሪካን ዲጂታልና የሥራ ፈጠራ መጻኢ ዕድል ለማብቃት የሚሠራ አህጉር አቀፍ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ የሥራ ፈጠራ ልማት መድረክ ነው። እንደ ኤ.ኤል.ኤክስ ቬንቸርስ (ALX Ventures) እና ፋውንደር አካዳሚ (Founder Academy) ባሉ ተነሳሽነቶች አማካኝነት፣ ሥራ ፈጣሪዎች ሊሰፉ የሚችሉ ጠንካራ የንግድ ድርጅቶችን እንዲገነቡ የቴክኖሎጂ ሥልጠና፣ የሥራ ፈጣሪዎች አቅም ግንባታ፣ የማማከር አገልግሎት፣ እንዲሁም የጀማሪ ድርጅቶች ማብቂያ (Incubation) እና ማፋጠኛ (Acceleration) አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ለሚዲያ መረጃ እና ጥያቄዎች፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH)፣ የካማ ኮሙኒኬሽን ቡድን
ኢሜይል፡ dagmawi.zeleke@eih.et ፣ info@kama.et
ስልክ ቁጥር፡ +251 911 181 353 ፣ +251 937 631 717
ድረ-ገጽ፡ kama.et