አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ – የካቲት 08፣ 2017– ዳንጎቴ ግሩፕ የተሰኘው የአፍሪካ ግንባር ቀደም ኢንዱስትሪያል ኩባንያ እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በጋራ በመሆን በዛሬው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ያሉት ፕሮጀክቶቹ ላይ እያከናወነ ያለውን ከፍተኛ የማስፋፊያ ስራ አሳውቀዋል። ይህም የሀገሪቱ መስህብ በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ማሳያ ሆኗል።
የዳንጎቴ ግሩፕ ሊቀመንበር እና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሊኮ ዳንጎቴ ስለ አዲሱ ኢንቨስትመንት አቅጣጫቸው ሲናገሩ፡ “ሁሌም በኢትዮጵያ በሚኖረኝ ጉብኝት ደስተኛ ነኝ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረግኩት ጉብኝትና ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረግሁት ውይይት፣ በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ለውጦችን ሳይ ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት ተነሳስቻለሁ። በሙገር የሚገኘው 2.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ፋብሪካችን ከፕሮጀክቶቻችን አንዱ እና ዋነኛው ነው። ውጣ ውረዶች ቢያጋጥመንም በዚህ ኢንቨስትመንት በጣም ደስተኛ ነኝ” በማለት “100% ብድር እና 100% የትርፍ ድርሻን በተሳካ ሁኔታ ወደ ሀገር ቤት መመለሳችንን በደስታ እገልጻለሁ” ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
አቶ ዳንጎቴ በአፍሪካ ውስጥ ካሉት ትላልቅ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውን ‘የዳንጎቴ ማጣሪያ’ በተሳካ ሁኔታ ሥራ ካስጀመሩ በኋላ ትልልቅ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለማቆም አቅደው ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መገናኘታቸው አመለከታቸውን እንደለወጠው ገልጸዋል። በመሆኑም ዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ ያለውን የሲሚንቶ የማምረት አቅሙን በእጥፍ ለማሳደግ ዝግጁነቱን አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ በበኩላቸው የማስፋፊያ ስራውን በደስታ መቀበላቸውን ተናግረው ኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ እድገትን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት ሲገልፁ “ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለኢንቨስትመንት እና ለስራ እድል ፈጠራ ቅድሚያ የሚሰጥ የኢኮኖሚ ለውጥ እያስመዘገበች ነው። ይህን ተከትሎ ዳንጎቴ ግሩፕ በአገራችን አሻራውን ሲያሰፋ በማየታችን ተደስተናል። ይህ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ የንግድ አካባቢ ላይ የመተማመን ምልክት ሲሆን ለመሰረተ ልማት እና ለኢኮኖሚ እድገታችን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል” ብለዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከተነሱ ቁልፍ ነጥቦች መካከል
● ሙገር የሚገኘውን የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ አዲሱ ማስፋፊያ የፋብሪካውን የማምረት አቅም በአመት ወደ 5 ሚሊዮን ቶን ይጨምራል።
● ዳንጎቴ ግሩፕ በናይጄሪያ 60,000 ሄክታር መሬት ላይ የሚሸፍነውን የስኳር ልማት ልምዱን በመከተል በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለማስፈር በኢትዮጵያ ያለውን የኦሞ ኩራዝ ስኳር ኩባንያ ያስፋፋል።
● የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዳው የሀገሪቱ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከተፈጠረ በኋላ በኢትዮጵያ የዩሪያ ማምረቻ ፋብሪካን ለመትከል ታስቧል።
አቶ ዳንጎቴ የአህጉሪቱን እድገት ለመምራት ‘የአፍሪካ የንግድ መሪዎች’ ያላቸው ሚና ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል፡ “አፍሪካ የምትለማው በአፍሪካውያን ነው። የፖለቲካ መሪዎቻችን የአፍሪካ ህብረትን ለማጠናከር በሚሰሩበት ወቅት፣ እኛ ደግም የንግድ መሪዎች እንደመሆናችን መጠን በአህጉሪቱ ያለውን የንግድ ትስስራችንን በማጠናከር ጥረታቸውን መደገፍ አለብን” ብለዋል።
እነዚህ ኢንቨስትመንቶች የዳንጎቴ ግሩፕን በአፍሪካ ቀዳሚ ሲሚንቶ የማምረት አጠቃላይ አቅሙን በዓመት ወደ 55 ሚሊዮን ቶን ያሳድጋል። በኢትዮጵያ የስኳር እና ማዳበሪያ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም የስራ እድል ፈጠራን፣ የግብርና ምርታማነትን እና የኢንዱስትሪ ልማትን ይደግፋል።